የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን ለማርገብ የሚያስችል የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ይፋ አደረገ።
የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያውን አስመልክቶ የባንኩ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የዋጋ ንረትን በሁነኛ መልኩ እና በቀጣይነት ለመቆጣጠር የብሔራዊ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ጠንካራ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ማድረጉን ተናግረዋል።
ከውሳኔዎቹ መካከል የሀገር ውስጥ ብድር ዕድገት በ14 በመቶ ጣሪያ እንደሚገደብ ጠቅሰው፤ ይህም ሁሉም ንግድ ባንኮች የብድር ዕድገት ዕቅዳቸው በዚህ የብድር ጣሪያ መሰረት እንዲስተካከል የሚያስገድድ መሆኑን አንስተዋል።
ለመንግስት የሚሰጠው የቀጥታ ብድር ባለፈው በጀት ዓመት ከተሰጠው ከአንድ ሦስተኛ እንዳይበልጥ የፖሊሲ ውሳኔ መተላለፉንም ይፋ አድርገዋል።
ባንኮች የገንዘብ እጥረት ሲገጥማቸው ከብሔራዊ ባንክ ለሚወስዱት የብድር ፋሲሊቲ የሚከፍሉት ወለድ ከ16 በመቶ ወደ 18 በመቶ ከፍ እንዲል መወሰኑንም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ቁልፍ የሆኑ የወጪ ንግዶች ላይ የተሰማሩ ላኪዎች የውጭ ምንዛሬ የማስተላለፍ ግዴታ ከዚህ ቀደም ስራ ላይ የነበረው 70/30 የድርሻ ክፍፍል ወደ 50/50 እንዲሻሻል መደረጉንም ነው የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ የገለጹት።
በውሳኔው መሰረት ከአጠቃላይ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ውስጥ 50 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ እንደሚያስገቡ ተናግረዋል።